የክልሉ የዲሞክራሲ ተቋማት የጋራ ፎረም በሩብ ዓመቱ ያከናወናቸው ሥራዎች አበረታች መሆኑ ተገለፀ፡፡
(ጥቅምት፣17/2018 ዓ.ም) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ ፎረም በተያዘው በጀት ዓመት በሩብ ዓመቱ ያከናወናቸው ሥራዎች አበረታች መሆኑ ተገልጿል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ ፎረም ባለድርሻ አካላት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ የ1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትን በጥልቀት በመገምገም በቀጣይ ሩብ ዓመት መሰራት በሚገባቸው ሥራዎች ላይ ተወያይቷል።
የጋራ ፎረሙ በሩብ ዓመቱ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁና የመንግስት አገልግሎት ግልፀኝነት ፣ተጠያቂነትና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ ያከናወናቸው ሥራዎች አበረታች መሆኑ ተገልጿል።
የሰብአዊ መብት የአያያዝ ችግሮች እንዲስተካከሉና እንዲሻሻሉ የጀመራቸው ሥራዎችን ፎረሙ በቀጣይ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመድረኩ ተነስቷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ መለሰ ኪዊ በሩብ ዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም መከናወኑን ገልፀው ፤ለሥራው ውጤታማነትና የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል ከዲሞክራሲ ተቋማትና ተባባሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
በዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ ፎረሙ በየወቅቱ የሚከናወኑ ተግባራት የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም የተከበሩ አቶ መለሰ አሳስበዋል።
ሙስናን የሚፀየፍ ዜጋ ለመፍጠር ግንዛቤ ፈጠራ አስተምሮ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባም የተከበሩ አቶ መለሰ አንስተዋል።
በመጨረሻም ፎረሙ በቀጣይ ሩብ ዓመት ዕቅድ ላይ መካተት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
